ናሙና አመራረጥ (Sampling)
የጥናቱ አካል የሆነውን ስብስብ በሙሉ /1ዐዐ%/ መውሰድ በማይችልበት ሁኔታ ናሙና እንጠቀማልን፡፡ ናሙና ከአጠቃላይ ስብስብ (Population) ውስጥ ስብስቡን ለመወከል በሚመች መልክ ለጥናታዊ ምርምር የሚወሰድ የመረጃ ማግኛ ክፍል ነው፡፡ አብዘኛውን ጊዜ ናሙና የሚወሰደው በአጠቃላይ ስብስቡ ውስጥ ያሉ ጥናቱ የሚነካቸው ሰዎች ወይም ሁኔታዎች ብዛትና ስፋት ሲኖራቸውና ከጊዜ፣ ከገንዘብና ከሰው ኃይል አንፃር አንድ ላይ ለመጠናት የማይችሉ ሲሆን ነው፡፡
ናሙና በሁለት ዋና ዋና ዘርፎች ሊከፈል ይችላል፡፡ እነርሱም፡-
1. ግምት ሰጭ (Probability Sampling)
2. ግምት የማይሰጥ (Non-Probability Sampling)
I. ግምት ሰጭ (Probability Sampling)
ግምት ሰጭ ናሙና ከአጠቃላይ ስብስብ ውስጥ ለናሙናነት ለሚመረጡ ሰዎች ወይም ሁኔታዎች እኩል የመመረጥ እድል የሚሰጥ የናሙና አመራረጥ ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ሥር አራት የናሙና አይነት ይገኛሉ፡፡ እነርሱም፡-
- ነሲብ ናሙና (Simple Random Sampling)
- በሥርዓት የተዘጋጀ ናሙና (Systematic Sampling)
- የተከፋፈለ ናሙና (Stratified Sampling)
- ጥምር ናሙና (Cluster Sampling)
1. ነሲብ ናሙና (Simple Random) Sampling)
ነሲብ ናሙና ለእያንዳንዱ በጥናት የመታቀፍ ባሕርይ ላለው ሰው ወይም ሁኔታ እኩል የመመረጥ ዕድል የሚሰጥ የናሙና ዓይነት ነው፡፡ ለጥናቱ የሚመረጡ ሰዎች ወይም ሁኔታዎች በአንድ አጠቃላይ ስብስብ ውስጥ እስከሆኑ ድረስ ተመሳሳይ ወይም የማይመሳሰሉ ቢሆኑም የመመረጥ እድላቸው ተመጣጣኝ መሆን ይኖርበታል፡፡
2. በሥርዓት የተደራጀ ናሙና (Systematic Sampling)
ይህ ዓይነቱ ናሙና የተወሰነ የአመራረጥ ስልትን ተከትሎ የሚካሄድ ነው፡፡ ለምሳሌ:- ሊመረጡ የሚችሉ የሚገመቱ 1ዐዐ ተማሪዎች ቢኖሩና ከመካከላቸው 2ዐ በናሙናነት የሚወሰዱ ከሆነ ያሉት ተማሪዎች በሙሉ /1ዐዐ/ ዝርዝራቸው ተጽፎ ከአምስት አንድ ብቻ ተለቅመውቨ ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ በዚህ አሠራር 5ኛ፣ 1ዐኛ፣ 15ኛ፣ ….1ዐዐኛ ድረስ ያሉት 2ዐ ተማሪዎች ይመረጣ ማለት ነው፡፡
3. የተከፋፈለ ናሙና (Stratified Sampling)
አጥኝው ይህንን የናሙና አወሳሰድ ዘዴ ለመጠቀም በሚያሰብብበት ወቅት የተጠኚ ናሙናውን የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም በምድብ በምድብ በመከፋፈል የተወሰነ ወካይ ቁጥር ከየምድቡ የሚወስድበት ዘዴ ነው፡፡
ለምሳሌ ተማሪዎችን በትምህርት ውጤታቸው ከፍተኛ፣ መካከለኛ እና ዝቅተኛ ውጤት በማለትና በመከፋፈል ከእያንዳንዱ ምድብ ናሙና በመውሰድ መረጃውን የተሟላ ለማድረግ ወይም በነዚህ ባሕሪያት መካከል ያለውን ልዩነት ወይም ግንኙነት ለማጥናት ይጠቀምበታል፡፡ ወይንም ደግሞ አጣቃላይ የጥናቱን population ተመሳሳይ የሆኑትን በየክፍሉ ከፋፍሎ ናሙና መውሰድ ነው ። ለምሳሌ በአካባቢ (Demographic), የገቢ መጠን (Income level), የትምህርት ደረጃ (Educational level) ተጠቅመን ልንከፋፍል እንችላለን።
4. ጥምር ናሙና (Cluster Sampling)
ይህ ግምት ሰጭ የናሙና አይነት በናሙናዎች ቁጥር ላይ ሳይሆን አጠቃላይ ቡድንን በመምረጥ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ማለት ከበርካታ የተጠኚ የትኩረት ቡድኖች (ለምሳሌ ት/ቤት፣ ትም/ተቋም ሊሆን ይችላል) (Target Populations) መካከል የተወሰኑትን ትምህርት ቤቶች ወይም የትምህርት ተቋማት በ% በመውሰድ በውስጡ ያሉትን ተማሪዎች ወይም ተጠኝዎች በሙሉ በመውሰድ የጥናቱ አካል ወይም ተሳታፊ የሚያደርግ የናሙና አወሳሰድ ዘዴ ነው፡፡
II. ግምት የማይሰጥ ናሙና (Non-Probability Sampling)
ግምት የማይሰጥ ናሙና በጥናቱ ለመታቀፍ እንደሚችሉ የሚገመቱ ሰዎች ወይም ሁኔታዎች ለጥናቱ የመመረጥ እድላቸው ምን ያህል እንደሆነ የማያሳይ የናሙና ዓይነት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ናሙና በቀላል ወይ ባልተወሰነ ሁኔታ እንዲካሄድ ለሚፈለጉ ትናንሽ የመነሻ ጥናቶች የሚያገለግል ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ናሙና የሚካሄድ ጥናት ውጤት ሊሠራ የሚችለው በናሙናነት ለተመረጡ ሰዎች ወይም ሁኔታዎች ብቻ ነው፡፡ የጥናቱ ውጤት ከናሙናው ውጭ በአጠቃላይ ስብስብ ውስጥ ላሉት ሰዎች ወይም ሁኔታዎች ለማጠቃለል አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ግምት የማይሰጥ ናሙና በሦስት ዋና ዋና የናሙና አመራረጥ ስልቶች ይወሰዳል፡፡ እነርሱም የሚከተሉት ናቸው፡-
ሀ) የምቾት ናሙና (Convenience Sampling)
ለ) የድርሻ ናሙና (Quota Sampling)
ሐ) የታለመ ናሙና (Purposive Sampling)
- 4ቱ Probability Sampling በደንብ አይተናል። ስለ 3ቱ ግምት የማይሰጥ (Non-Probability Sampling Methods) እንማራለን።
1. የምቾት ናሙና (Convienience Sampling
ምቾት ናሙና በቅርብ በቀላሉ የሚገኙትን የመረጃ ምንጮች የሚጠቁም የናሙና ዓይነት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ መምህር በሚኖርበት ወረዳ ባሉት ቀበሌዎች በHIV ትምህርት ያላቸውን ግንዛቤ ለማጥናት ይፈልጋል፡፡ መምህሩ ለጥናቱ የሚያስፈልገውን መረጃ በቅርቡ በመኖሪያው አካባቢ ካሉት አምስት ቀበሌዎች ይሰበስባል፡፡ ይህ አይነቱ አሠራር ከምቾት አንፃር የሚካሄድ ይሆናል፡፡
2. የድርሻ ናሙና (Quota Sampling)
የድርሻ ናሙና ለአንድ ጥናትታዊ ምርምር ሊመረጡ እንደሚችሉ የሚገመቱ ከብዛታቸው የተነሳ በሁለት ወይም በበለጡ ምድቦች ሊከፈሉ ከሚችሉ ሰዎች ወይም ሁኔታዎች መካከል የተወሰኑትን ለመምረጥ የሚያገለግል የናሙና አመራረጥ ስልት ነው።
3. የታለመ ናሙና (Purposive Sampling)
የታለመ ሁነኛ ናሙና ተመራማሪው ጥናቱ ያቅፋቸዋል ተብለው ከሚገመቱ ሰዎች ወይም ሁኔታዎች መካከል በይበልጥ ለተመረጠው ርእስ ይስማማሉ ብሎ የሚገምታቸውን ለይቶ በመውሰድ የሚጠቀምበት የናሙና አመራረጥ ስልት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ መምህር በሚያስተምርበት ትምህርት ቤት የአስተዳደር ችግር በተመለከተ ጥናታዊ ምርምር ማካሄድ ይፈልጋል እንበል፡፡
ከዚህም የተነሳ መምህሩ ከሌሎች የመረጃ ምንጮች በተጨማሪ የትምህርት ቤቱን መምህራን እንደ መረጃ ምንጮች ለመጠቀም ያቅዳል፡ ከትምህርት ቤቱ 15ዐ መምህራን መካከል 2ዐ መምህራን በዩኒት መሪነትና በዲፓርትመንት ኃለፊነት የሚያገለግሉ ይሆናሉ፡፡ ይህን የሚያደርግበት ምክንያት በአስተዳደር ሥራ ተሳትፎ ያላቸውና የሌላቸው መምህራን በአንድነት ሊታዩ ስለማይችሉ ነው፡፡
Comments
Post a Comment